image
image
image
image
image

በአዲስ አበባ ከ300 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት የ7 ቢሊዮን ብር እሴት ያለው የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ይፋ ሆነ።

ጥቅምት 5, 2019
አዲስ አበባ| ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም| የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን "በጎነት ለአዲስ አበባ ከፍታ!" በሚል መሪ ቃል የ2019 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብርን በይፋ አስጀመረ። በመርሃ ግብሩ ከ300 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች በድግግሞሽ የሚሳተፉ ሲሆን፣ 7 ቢሊዮን ብር የሚገመት የመንግስት ወጪን በማዳን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ዛሬ በይፋ የተስጀመረው ይህ የበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ9 ዋና ዋና ፕሮግራሞች እና በ23 ንዑሳን መርሀ ግብሮች ተከፋፍሎ የሚተገበር ሲሆን፣ የበርካታ ወገኖችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል ያለመ ነው። መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ምክትልና የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከድር ማሞ ባደረጉት ንግግር፤ በተደመረ አቅም የበርካታ ዜጎችን ችግር በመቅረፍ መዲናዋ ያስመዘገበችው ሰው ተኮር ውጤት ለሌሎች ከተሞች በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም በዚሁ የበጋ መርሃ ግብር የህዝቡን አቅምና የከተማዋን ጸጋዎች በማስተባባር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። አቶ ከድር አያይዘውም የከተማዋ ነዋሪ በዲጂታል በጎነት መርሃ ግብር ወደ 6400 "A" በመላክ እንዲሁም በሌሎች የተዘጋጁ መርሃ ግብሮች ላይ በንቃት በመሳተፍ፣ የታቀዱት የበጎ ፈቃድ ፕሮግራሞች ዳር እንዲደርሱ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባባሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ት ጽዮን ደረጀ በበኩላቸው፤ በተጠናቀቀው የክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር የተተገበሩ ስራዎች የብዙዎችን የኑሮ ሸክም ከማቅለል ባሻገር እርስ በእርስ የመደጋጋፍ እሴትን በማሳደግ ለሀገራዊ አንድነት መጠናከር የላቀ ፋይዳ አበርክተዋል። ኮሚሽነሯ አክለውም በተጠናቀቀው የክረምት በጎ ፈቃድ ፕሮግራም የተከናወኑ ስኬቶችን የጠቀሱ ሲሆን ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱን፤ 4 ሺህ 227 ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ከ32 ሺህ በላይ አቅመ-ደካማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። በመጨረሻም ኮሚሽነር ወ/ት ጽዮን ደረጀ የከተማዋ ነዋሪዎች ዛሬ በይፋ በተጀመረው የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ላይ ከቀደመው በበለጠ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውንና ሀብታቸውን እንዲያውሉና በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

መልዕክትዎን ይላኩ